ስለ መከራ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች
ስለ መከራ የሚናገሩ ለማንበብ፣ ለማሰላሰል፣ እና ለመሸምደድ የሚሆኑ 12 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች።
የአሁኑ ዘመን መከራ ሊገለጥልን ካለው ክብር ጋር ሊነጻጸር እንደማይገባው አስባለሁ።
ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ ስትቀበሉ፣ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቍጠር አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ሐሴት አድርጉ።
የምህረት አባት፥ የመፅናናት አምላክ እና በመከራችን ሁሉ የሚያፅናናን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ። እግዚአብሔር በመከራችን ሁሉ ያፅናናል፥እኛም ራሳችን በእርሱ በእግዚአብሔር በተፅናናንበት መፅናናት ልክ ሌሎችን ማፅናናት እንችላለን።
ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን በመከራዎቻችን ደግሞ ደስ ይለናል። መከራ መጽናትን እንደሚያደርግ እናውቃለን። መጽናት ተቀባይነትን፥ ተቀባይነትም ስለ ወደፊቱ መተማመኛን ያስገኛል።
ምክንያቱም ከክርስቶስ የተነሳ ይህ የተሰጣችሁ አገልግሎት በእርሱ እንድታምኑ ብቻ ሳይሆን በእርሱ ምክንያት መከራ እንድትቅበሉም ጭምር ነው።
የተጠራችሁት ለዚህ ነው፤ ክርስቶስ ስለ እናንተ መከራን የተቀበለው የእርሱን ፈለግ እንድትከተሉ ምሳሌ ሊተውላችሁ ነው።
ምክንያቱም የክርስቶስ መከራ በእኛ ላይ እንደበዛ፥ መፅናናታችንም በክርስቶስ በኩል እንዲሁ ይበዛልናል።
ይኸውም እርሱን የማወቅ ጽድቅ፤ የእርሱ የትንሣኤ ኃይልና የመከራው ተካፋይ የመሆንና በሞቱም ክርስቶስን ለመምሰል ነው።
ለጥቂት ጊዜ መከራ ከተቀበላችሁ በኋላ ፣ በክርስቶስ ወደ ዘለዓለማዊ ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችኋል ፤ ያበረታችኋልም።
ልጆች ከሆንን ወራሾችም ነን፥ማለትም የእግዚአብሔር ወራሾች ነን። ከእርሱ ጋር እንድንከብር በርግጥ አብረነው ደግሞ መከራን ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን የምንወርስ ነን።
ብንጸና ከእርሱ ጋር እንነግሣለን፡፡ ብንከዳው እርሱ ደግሞ ይክደናል፡፡
ኢየሱስ ራሱ መከራ የተቀበለና የተፈተነ በመሆኑ፣ የሚፈተኑትን ሁሉ ሊረዳቸው ይችላል።