ስለ መከራ የተቀበለው አገልጋይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች
ስለ መከራ የተቀበለው አገልጋይ የሚናገሩ ለማንበብ፣ ለማሰላሰል፣ እና ለመሸምደድ የሚሆኑ 10 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች።
የተናቀ ከሰውም የተጠላ፣ የሕማም ሰው ደዌንም የሚያውቅ ነው። ሰውም ፊቱን እንደሚሰውርበት የተናቀ ነው፣ እኛም አላከበርነውም።
እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፣ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፣ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።
ተጨቆነ፣ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት፣ በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ፣ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።
ፊቱ ከሰዎች ሁሉ ይልቅ፣ መልኩም ከሰዎች ልጆች ይልቅ ተጐሳቍሎአልና ብዙ ሰዎች ስለ አንተ እንደ ተደነቁ፣ እንዲሁ ብዙ አሕዛብን ያስደንቃል፤
የባሪያንም መልክ ያዘ፤ በሰው አምሳል ተገለጠ፤ እንደ ሰውም ሆኖ በትህትና ራሱን ዝቅ አደረገ። እንዲሁም እስከ ሞት፤ያውም እስከ መስቀል ሞት ድረስ ታዛዥ ሆነ።
በእውነት ደዌያችንን ተቀበለ ሕመማችንንም ተሸክሞአል፤ እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።
እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።
እግዚአብሔርም በደዌ ያደቅቀው ዘንድ ፈቀደ፤ ነፍሱን ስለ ኃጢአት መሥዋዕት ካደረገ በኋላ ዘሩን ያያል፣ ዕድሜውም ይረዝማል፣ የእግዚአብሔርም ፈቃድ በእጁ ይከናወናል።
ጀርባዬን ለገራፊዎች፣ ጕንጬንም ለጠጕር ነጪዎች ሰጠሁ፣ ፊቴንም ከውርደትና ከትፋት አልመለስሁም።
ከነፍሱ መከራ በኋላ፣ ብርሃን ያያል ደስም ይለዋል፤ ጻድቅ ባሪያዬም በእውቀቱ ብዙ ሰዎችን ያጸድቃል፣ ኃጢአታቸውን ይሸከማል።